ጤነኛ

ከ21 ሰዎች ውስጥ አንዱ በደንዳኔ(ኮለን) ካንሰር ይያዛል። እራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንችላለን?

የደንዳኔ ካንሰር ከቅርብ ግዜ ጀምሮ በዜና ላይ መስማት የተለመደ ሁኗል። ምክንያቱ እድሜአቸው ከ50 አመት በታች የሆኑ ሰዎች ላይ የመከሰት እድሉ እየጨመረ በመምጣቱ ነው። የጭማሪው ምክንያት ምን እንደሆነ በቅጡ አይታወቅም። የተመጣጠነ ምግብ ባለመመገብ እንዲሁም አካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለማድረግ ምክንያት ነው ተብሎ ይታሰባል።

የኮለን እና የሬክታል ካንሰሮች ከባድ በሽታ ቢሆኑም ጥንቃቄዎችን በመውሰድ ልንከላከላቸው የምንችላቸውው በሽታዎች ናቸው።

ኮሎሬክታል ካንሰርን እንዴት መከላከል እንችላለን

እንደ ሌሎች ካንሰሮች ሲጋራ ማጨስ ማቆም ለዚህ የካንሰር አይነት ያለንን ተጋላጭነት ይቀንሳል። የሚያጨሱ ከሆነ ከዛሬ ጀምሮ ማቆም ይኖርብዎታል።

አመጋገብ ሌላ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነገር ነው። ቀይ ስጋ አብዝቶ መመገ ተጋላጭነታችንን ይጨምራል። በቀን ከአንድ በላይ አልኮል መጠጥ መጠጣትም በበሽታው የመያዝ እድላችንን ይጨምራል።

በሌላ በኩል ፋይበር አብዝቶ በመመገብ ተጋላጭነታችንን መቀነስ እንችላለን። ፍራፍሬ እና አትክልት ማዘውተር ለበሽታው ያለንን ተጋላጭነት ይቀንሳል። በሽታው ከፍተኛ የሰውነት ክብደት ያላቸው ሰዎች ላይ ይጨምራል። በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግ ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ ያደርገናል። በየቀኑ ለ20 ደቂቃ መሃከለኛ ጥረት የሚጠይቅ እንቅስቃሴ ማድረግ ተጋላጭነታችንን ከ25 እስከ 50 በመቶ ይቀንሳል።

እድሜ በገፋ ቁጠር ለበሽታው ያለን ተጋላጭነት ይጨምራል። ነገር ግን በሽታው ያለምንም ምልክት በየትኛውም እድሜ ሊከሰት ስለሚችል አልፎ አልፎ ምርመራ ማድረግ ይመከራል። ኮለኖስኮፒ ምርመራ ማካሄድ በሽታው አለመፈጠሩን የምናረጋግጥበት አንዱ መንገድ ነው።

ምርመራ

ኮሎሬክታል ካንሰር በድንገት አይፈጠርም። የሚጀምረው ፖሊፕ ተብሎ በሚጠራ ኮለን ውስጥ በሚፈጠር ትንሽ እብጠት ነው። ይህ እብጠት ብዙ ግዜ የህመም ስሜት አይፈጥርም። ነገር ግን ከብዙ አመታት በኋላ ወደ ካንሰርነት ሊቀየር ይችላል። መፈጠሩን ማወቅ የሚቻለው ምርመራ በማካሄድ ነው።

በምርመራ ግዜ እብጠቱ መፈጠሩ ከታወቀ እብጠቱን በቀላሉ በማስወገድ ካንሰር የመፈጠር እድሉን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ይቻላል። ከ45 አመት እድሜ ጀምሮ ኮለኖስኮፒ ምርመራ ማድረግ ይመከራል። አንዴ ምርመራውን ያካሄደ ሰው ለ10 ሳይመረመር መቆየት ይችላል።

በሽታው በቤተሰብ ውስጥ ያለባቸው ሰዎች በግዜ ምርመራ መጀመር አለባቸው።

የኮሎሬክታል ካንሰር ምልክቶች

ብዙ ግዜ ምልክት ባይኖረውም ኮሎሬክታል ካንሰር አልፎ አልፎ ምልክት ያሳያል። ሰገራ ውስጥ ደም ከታየዎት ግዜ ሳይሰጡ ዶክተር ጋር መሄድ ይኖርብዎታል።

የሰገራ ውስጥ ደም የተለያዩ መንስኤዎች አሉት። ደም ካየን የደንዳኔ ካንሰር ተፈጥሯል ማለት አይደለም። ቢሆንም ግን ምርመራ ማካሄድ ተገቢ ነው። የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ የሚጸዳዱበት ሰአት ለውጥ እና የሰገራ መልክ ለውጥ ማሳየት ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ ምርመራ ማካሄድ ተገቢ ነው።

በበሽታው ብያዝስ

ኮሎሬክታል ካንሰር በንጽጽር የተሻለ ህክምና አማራጮች ያሉት የካንሰር አይነት ነው። በቀዶ ጥገና የተፈጠረበትን አካባቢ በማስወገድ ህክምና ይደረጋል። በሽታው የገፋ ከሆነ ግን አብሮ ኪሞቴራፒ ማድረግ ያስፈልጋል።

ተገቢውን ጥንቃቄ እና ቅድመ-ምርመራ በማድረግ በከፍተኛ ደረጃ ልናስቀረው የምንችለው በሽታ ነው። ኮለኖስኮፒ ሊያደርጉ የሚገቡ ሰዎች ምርመራውን ቢያደርጉ በሽታውን በ85 በመቶ መቀነስ ይቻላል።

Tenegna

አነጋግሩን

ከእርስዎ መስማት እንፈልጋለን። እባክዎ አነጋግሩን።

በጣም የታዩ