ጤነኛ

ችላ ማለት የሌለብዎ የሆድ ቁስለት(አልሰር) ምልክቶች

አልሰር(Ulcer) ወይም የሆድ ቁስለት ሆድ ወይም ትንሹ አንጀትን እየበላ የሚሄድ በሽታ ሲሆን የሰውነት ውስጥ ደም መፍሰስ ወይም ከባድ ኢንፌክሽን ሊፈጥር ይችላል። የሚከተሉትን ምልክቶች በማወቅ ከመርፈዱ በፊት አልሰርን መያዝ ይቻላል።

የላይኛው የሆድ ክፍል ላይ ህመም

የአልሰር ዋነኛ ምልክት የላይኛው የሆድ ክፍል ላይ የሚፈጠር የህመም ስሜት ነው። ብዙ ሰው ህመሙ የሚፈጠረው ሆድ ወይም ትንሹ አንጀት ያሉበት ቦታ ላይ ይመስለዋል። ነገር ግን ብዙ ግዜ ህመሙ የሚሰማን በጡት አጥንት እና እምብት መሃከል ነው። የማቃጠል፣ የመቁረጥ ወይም የመደንዘዝ ስሜት ሊሰማን ይችላል። ህመሙ ሲጀምር በትንሹ ይሆንና አልሰሩ እየጨመረ ሲሄድ ህመሙ አብሮ እየጨመረ ይሄዳል።

የማቅለሽለሽ ስሜት

ሌላኛው የአልሰር ምልክት የማቅለሽለሽ ስሜት ነው። አልሰሮች የሆዳችንን የኬሚካል ይዘት ይቀይሩታል። በዚህም ምክንያት ምግብ ሲፈጭ የህመም ስሜት ሊፈጠር ይችላል።

ማስመለስ

አልፎ አልፎ የማቅለሽለሹ ስሜት ይብስና ያስመልሰናል። ማስመለስ የህመም ስሜት የሚፈጥር ቢሆንም እንደ አስፕሪን እና ኢቡፕሮፊን ያሉ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን መውሰድ የለብንም። እነዚህ መድሃኒቶች የአልሰር ተጋላጭነታችንን ይጨምሩታል።

በሰገራ ግዜ መድማት

ከሰገራ ጋር የተቀላቀለ ደም የተለያዩ በሽታዎች ምልክት ሊሆን ሊሆን ይችላል። ነገር ግን መድማት የላይኛው የሆድ ክፍል ላይ ከሚፈጠር ህመም ጋር አብሮ ሲፈጠር ብዙ ግዜ የአልሰር ምልክት ነው። ብዙ ግዜ ትውከት ወይም ሰገራ ውስጥ ደም ይቀላቀላል። ሰገራ ሊጠቁር ይችላል። እነዚህ ህመም ስሜቶች ሲፈጠሩ አልሰር መሆኑን ለማረጋገጥ የደም ምርመራ ወይም ኢንዶስኮፒ ይደረጋል። የሰገራ ደም የመቀመጫ ኪንታሮት ወይም የኮለን ካንሰር ምልክት ሊሆን ስለሚችል ምርመራ ማካሄድ ተገቢ ነው።

ከምግብ በኋላ የቃር ስሜት

ምግብ በተመገቡ ቁጥር የቃር ስሜት የሚሰማዎ ከሆነ አልሰር ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል። አልሰር ያለባቸው ብዙ ሰዎች ከፍተኛ የደረት ህመም ይሰማቸዋል። ማግሳት ወይም ስቅታ ሊፈራረቅብዎ ይችላል። እነዚህ ምልክቶች በቀናት ውስጥ ለውጥ ካላሳዩ ዶክተር ጋር መሄድ ይመከራል።

የሆድ መነፋት

ሆድ ከተለመደው በላይ ከተነፋ የአልሰር ምልክት ሊሆን ይችላል። የሆድ መነፋት የአልሰር አንዱ ቀዳሚ ምልክት ነው። የሆድ መነፋት ብቻውን የበሽታ ምልክት ላይሆን ይችላል። መነፋት ለሆድ የማይስማማ ነገር በመመገብ እንዲሁም በውሃ እጥረት ምክንያት ሊፈጠር ይችላል። ከላይ ከተጠቀሱት ምልክቶች ጋር አብሮ ከተፈጠረ ግን ዶክተር ማማከር ተገቢ ነው።

የምግብ ፍላጎት መጥፋት

አልሰር ሲፈጠር ብዙ ግዜ የምግብ ፍላጎት ይጠፋል። ይህ የሚያስከትለው የምግብ መቀነስ ከማስመለስ ጋር አብሮ ክብደት እንድንቀንስ ሊያደርገን ይችላል። አንዳንድ የአልሰር በሽታ ታካሚዎች ተመሳሳይ የምግብ መጠን እየበሉም ክብደት እንደቀነሱ ይናገራሉ። አልሰር ብቻውን ክብደት እንድንቀንስ ሊያደርገን ይችላል።

ለየት ያለ የረሃብ ስሜት

አልሰር የሚፈጥረው ህመም ከረሃብ ስሜት ጋር ሊምታታ ይችላል። መመገብ ሲጀምሩ ህመሙ ሊቀንስ ይችላል። እነዚህ ምልክቶች የሚታዩት አልሰር ትንሹ አንጀት ውስጥ ሳይሆን ሆድ ውስጥ በሚፈጠርበት ግዜ ነው።

የጀርባ ህመም

አልሰሩ ሆድን ከበሳ ጀርባ ላይ ህመም ሊፈጠር ይችላል። በዚህ ግዜ ህመሙ ከፍተኛ፣ ለረጅም ግዜ የሚቆይ እና ለማስታገስ አስቸጋሪ ይሆናል።

ማግሳት

ከመጠን በላይ የሚያገሱ ከሆነ የአልሰር ምልክት ሊሆን ስለሚችል ዶክተር ያማክሩ።

Tenegna

አነጋግሩን

ከእርስዎ መስማት እንፈልጋለን። እባክዎ አነጋግሩን።

በጣም የታዩ