ጤነኛ

ስለ ኩላሊት ጠጠር ማወቅ ያለብዎ ነገሮች

ኩላሊት ጠጠር ምንድን ነው?

ኩላሊት ቆሻሻን ከደም ሲያጣራ ሽንት ይፈጠራል። አንዳንድ ግዜ ሽንት ውስጥ የሚገኝ ጨው እና ሌሎች ንጥረነገሮች ይጣበቁና ጠጠር ይፈጥራሉ። እነዚህ ጠጠሮች ሲያንሱ የስኳር እንክብል ያህል ሲገዝፉ ደግሞ የቴብል ቴኒስ ኳስ ያህል ሊተልቁ ይችላሉ። ከተፈጠሩበት ቦታ ተላቀው ወደ ሽንት መስመር ከገቡ ከፍተኛ ህመም ሊፈጥሩ ይችላሉ።

የኩላሊት ጠጠር ምልክቶች

mohamed_hassan / Pixabay

ኩላሊት ጠጠር ወደ ሽንት ቧንቧ ሲያልፍ የሚከተሉትን ምልክቶች ሊፈጥር ይችላል።

  • ጀርባ፣ ሆድ ወይም ብሽሽት ላይ ከፍተኛ ህመም
  • ደጋግሞ ሽንት ቤት መሄድ
  • ሽንት ውስጥ ደም
  • ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ

ትናንሽ ጠጠሮች ያለችግር በሽንት ሊወጡ ይችላሉ።

ኩላሊት ጠጠር ነው ሌላ በሽታ

ጀርባ እና እምብርት ላይ ድንገተኛ እና ከባድ ህመም ከተሰማዎ በፍጥነት ወደ ዶክተር መሄድ አለብዎ። የሆድ ህመም እንደ ትርፍ አንጀት አይነት የሌላ በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል። በሽንት ግዜ የሚፈጠር ህመም ደግሞ የሽንት መስመር ኢንፌክሽን ወይም የአባላዘር በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል።

የቤት ውስጥ መፍትሄዎች

silviarita / Pixabay

የጠጠሩ መጠን ትንሽ ከሆነ የህመም ክኒን እየወሰዱ በሽንት መልክ እስኪወጣ እንዲጠብቁ ሊታዘዙ ይችላሉ። በዚህ ግዜ በቂ ውሃ እና ፈሳሾችን መጠጣት ይመከራል። ከ8-10ብርጭቆ ውሃ።

በሽንት መልክ ይውጣ የሚባለው የጠጠሩ መጠን ምን ያህል ሲሆን ነው

የጠጠሩ መጠን ከ5ሚሊሜትር በታች ከሆነ በራሱ የመውጣት እድሉ ከ90ፐርሰንት በላይ ነው። ከ5ሚሊሜትር እስከ 10ሚሊሜትር ከሆነ በራሱ የመውጣት እድሉ 50በመቶ ነው። ከዛ በላይ ከሆነ ብዙ ግዜ በህክምና እንዲወጣ ይደረጋል።

ህክምና

የሽንት ቧንቧ እንዲላላ በማድረግ ጠጠር በቀላሉ እንዲወጣ የሚያግዙ መድሃኒቶች አሉ። እነዚህ መድሃኒቶች አልፋ-ብሎከርስ የሚል ስያሜ አላቸው። እንደ ራስምታት እና ማዞር አይነት ሳይድ ኢፌክሽ ሊኖራቸው ይችላል።

የኩላሊት ጠጠር መንስኤ ምንድን ነው

በኩላሊት ውስጥ ያለው የውሃ፣ ጨው እና ንጥረነገሮች ቅልቅል ላይ ለውጥ ሲፈጠር ጠጠር ሊከሰት ይችላል። ይህ ለውጥ የተለያዩ መንስኤዎች አሉት። የሚበሉት ምግብ እና መጠጥ ወይም በሰውነትዎ የተፈጠረ ሌላ በሽታ ለኩላሊት ጠጠር መፈጠር መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ።

ቅድመ-ጥንቃቄዎች

የኩላሊት ጠጠር ዋነኛ መንስኤ በቂ ውሃ አለመጠጣት ነው። የሚመገቡት ምግብ ሌላ መንስኤ ነው። ብዙ የእንስሳ ፕሮቲን እና ሶዲየም መመገብ በአንዳንድ ሰዎች ላይ የኩላሊት ጠጠር የመፈጠር እድልን ይጨምራል። ጣፋጭ መጠጦችን አብዝቶ መጠጣት፣ ክብደት መጨመር እንዲሁም አንዳንድ መድሃኒቶችን መውሰድ ተጋላጭነትን ይጨምራል።

(Feature image by Jakupica [CC BY-SA 4.0 (https://creativecommons.org/licenses/by-sa/4.0)], from Wikimedia Commons)

Tenegna

አነጋግሩን

ከእርስዎ መስማት እንፈልጋለን። እባክዎ አነጋግሩን።

በጣም የታዩ