ጤነኛ

ስለ ግብረስጋ ግንኙነት በተለምዶ የሚነሱ 5 የተሳሳቱ አመለካከቶች

ሁላችንም በተለይ በታዳጊ እድሜአችን እያለን ስለ ግንኙነት የተሳሳቱ ነገሮችን እናምናለን። አንዳንድ የተሳሳቱ አመለካከቶች እርማት ሳያገኙ በበሳል እድሜአችን እራሱ አብረውን ይቆያሉ። የግብረስጋ ግንኙነት ህይወታችን ላይ ተጽእኖ መፍጠራቸውም አይቀርም። በዚህ ጽሁፍ በተለምዶ ስለሚታመኑ ግን የተሳሳቱ አምለካከቶችን እናያለን።

“ድንግላናዋን ያጣችው ወሲብ ሰለፈጸመች ነው”፣ “ግላዊ ወሲብ አይን ያጠፋል”፣ “ጥሩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወሲብ መቀነስ ያስፈልጋል።” እነዚህ አመለካከቶች በተለምዶ የሚሰሙ ናቸው። ግን ምን ያህል እውነታ አላቸው?

1) ሴት ልጅ ድንግልናዋን ልታጣ የምትችለው በወሲብ ብቻ ነው

ulleo / Pixabay

አንዲት ሴት ድንግላናዋን ካጣች ከዚህ በፊት ግንኙነት ፈጽማለች የሚለው አመለካከት በብዙዎቻችን ዘንድ አለ። ይህ አመለካከት በብዙ ባህሎች ዘንድ የሚገኝ ቢሆንም ሁሌም ትክክለኛ አመለካከት ነው ማለት አይቻልም።

የድንግልና አካል ከሴት ብልት ክፍተት ገባ ብሎ የሚገኝ ሜምብሬይን ሲሆን፣ ቅርጽና መጠኑ ከሰው ሰው ይለያያል። ይህ ሜምብሬይን ሳይኖራቸው የሚወለዱ ሴቶች በርካታ ናቸው። ጫና የበዛበት እካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሴቶች በእንቅስቃሴ ወቅት በሚፈጠር መሰንጠቅ የድንግላናቸውን አካል ሊያጡ ይችላሉ።

ብዙ ግዜ በግንኙነት ወቅት በሚፈጠር የድንግልና አካል መሰንጠቅ መድማት ይፈጠራል። ነገር ግን ይህ አካል የተለጣጭነት ባህሪ ስላለው በብዙ ሴቶች ዘንድ ከግንኙነት በኋላም ሳይሰነጠቅ ይቆያል። ሲሰነጠቅም የማይደማበት ግዜአቶች በርካታ ናቸው።

በአጠቃላይ ይህ አካል በተለያዩ ሴቶች የተለያየ ገጽታና ባህሪ ያለው ነው።

2) ወር አበባ ወቅት አቅራቢያ በሚደረግ ግንኙነት እርግዝና አይፈጠርም

DigitalMarketingAgency / Pixabay

አንድ ሴት ወር አበባ በምታይበት ግዜ እና ከግዜው በኋላ በሚከተሉት የተወሰኑ ቀናት ግንኙነት ብትፈጽም አታረግዝም የሚል ሃሳብ አለ። የተወሰነ እውነታ አለው። በዚህ ግዜ ግንኙነት ማድረግ ብዙ ግዜ ለእርግዝና አይዳርግም። ቢሆንም የማርገዝ እድሉ አሁንም አለው።

በዚህ ግዜ የማርገዝ እድል በሴትዋ የወር አበባ ግዜ ይወሰናል። በአብዛኛው ሴት ሙሉ የወር አበባ ዙር 28 ቀን ነው። በዛ ግዜ ከ3ቱ-5ቱ ቀናት ወር አበባ የሚታይበት ግዜ ነው። የወር አበባ ማለት የሴት ልጅ እንቁላል ከሌሎች የሴል ክምችቶች ጋር በወር አንዴ የሚወገድበት የደም ፈሰት ነው።

ሴት ለጽንስ በጣም ዝግጁ የምትሆነው ወር አበባ ከመታየት ከ12-16ቀን በፊት ባለው ግዜ ነው። አንዳንድ ሴቶች ግን አጭር የወር አበባ ዙር አላቸው። እነዚህ ሴቶች ለጽንስ ዝግጁ የሚሆንበት ግዜ ከሌላው ቀደም ብሎ ነው።

ከዛም አልፎ የወንድ ዘር ለ5 ቀናት በህይወት የሴትዋ ማህጸን ውስጥ መኖር ይችላል። ማህጸን ውስጥ ያለ የወንድ ዘር ቀኑን ጠብቆ ከሴትዋ እንቁላል ጋር በመዋሃድ ጽንስ ሊፈጥር ይችላል።

ስለዚህ ለማርገዝ ካልፈለጉ ከወር አበባ ግዜ ይልቅ ኮንዶም ወይም ሌላ የወሊድ መከላከያ መጠቀም ተገቢ ነው።

3) በግንኙነት ብቻ ነው መርካት የምትችለው

ean254 / Pixabay

አንድ ሴት ስሜት ጣሪያ ልትደርስ የምትችለው በግንኙነት እንቅስቃሴ ብቻ ነው ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን “ኢሴንሻልስ ኦፍ ኦብስቴትሪክስ ኤንድ ጋይናኮሎጂ” በሚል መጸሃፍ በተሰራ ጥናት በወንድ እና ሴት ብልት ንክኪ በሚፈጠር ስሜት የስሜት ጣሪያ ደርሰናል የሚሉት የሴቶች ብዛት 25ፐርሰንት ብቻ ነው። 75ፐርሰንቱ የስሜት ጣሪያ ለመድረስ የሴት ብልት ጫፍ ላይ የሚገኘው ክሊቶሪስ የሚባለው አካል ጋር ንክኪ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።

ፍቅረኛሞች ግዜ ወስደው የፍቅረኛቸውን አካል በደምብ ማወቅ አለባቸው። እርስ በእርስ የሚያስደስታቸውን ነገር ተነጋግረው ማወቅ እና አዲስ ነገር መመኮር ለጤነኛ የግንኙነት ህይወት አስፈላጊ ነው።

4) ግላዊ ወሲብ መጥፎ ነው

Free-Photos / Pixabay

ግላዊ ወሲብ እንደአጸያፊ እና መጥፎ ነገር ይታያል። ብዙ የጤና ችግሮችም እንድሚያመጣ ይነገራል። አይነስውር ያደርጋል እና በግንኙነት ወቅት መቸገር ያመጣል ተብሎ ይታሰባል።

ነገር ግን በብልት እና በአይን መሃከል ምንም አይነት ግንኙነት የለም። ብልትዎ ጋር በሚደረግ ንክኪ አይንዎት ምንም አይነት አደጋ አይጋረጥበትም።

እንደ ስፔሻሊስቶች ከሆነ ግላዊ-ወሲብ ምንም ያህል ቢደጋገም ምንም አይነት የጤና ችግር እንደማያመጣ ይናገራሉ። እንደውም የተለያዩ ጥቅሞች እንዳሉት የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ጫና እና ጭንቀትን ለመቀነስ እና ለሴቶች በወር አበባ ወቅት ለሚመጣ የማህጸን ጡንቻ መሳሳብ ለማስታገስ እንደሚጠቅም ይነገራል።

ግላዊ ወሲብ ግንኙነት ግዜ መቸገር ያመጣል የሚለውም ሃሳብ ከእውነት የራቀ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

5) ግንኙነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ያዳክማል

ግንኙነት ከፍተኛ ሃይል የሚጠይቅ እንቅስቃሴ እንደመሆኑ ሌላ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሰው ላይ ድካም በማምጣት ሙሉ ብቃቱን እንዳይጠቀም ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል።

ለብዙ አመታት የአትሌት አሰልጣኞች አትሌሎታቻቸውን ከውድድር በፊት ግንኙነት እንዳያደርጉ ሲከለክሉ ቆይተዋል። ይህ ፍራቻ ግን በመረጃ የተደገፈ አይደለም። በቅርብ የወጡ ጥናቶች እንደሚናገሩት ስፖርታዊ ውድድር ከማድረግ በፊት የሚደረግ ግንኙነት የአቋም መዋዠቅ እንደማይፈጥር ይናገራሉ። ቢሆንም ተመራማሪዎች ይበልጥ ምርምር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

Tenegna

አነጋግሩን

ከእርስዎ መስማት እንፈልጋለን። እባክዎ አነጋግሩን።

በጣም የታዩ