ጤነኛ

የገብረ ስጋ ግንኙነት ጭንቀት። እንዴት ፍራቻዎን ማሸነፍ ይችላሉ?

የግብረስጋ ግንኙነት ሃፍረት ወይም ፍራቻ በማንኛውም እድሜ ያለን ማንንም ሰው ሊያጠቃ የሚችል ነገር ነው። በማንኛውም እድሜ ያለ ወንድም ሆነ ሴት ሊቸገር ይችላል።

ለአንዳንድ ሰዎች የግንኙነት ጭንቀት ለአጭር ግዜ የሚቆይ ነገር ሲሆን በሌሎች የግንኙነት ህይወታቸውን ለረጅም ግዜ የሚረብሽ ይሆናል።

የግንኙነት ጭንቀት እንዴት ነው የሚገለጸው? እንደ ግንኙነት ሃኪም ክላውዲያ ሲክስ ችግሩ በሴቶች እና ወንዶች ላይ የተለያየ መገለጫ አለው። ሁለቱም ጾታዎች የሚጋሩት ስሜት ቢኖር እራሳቸውን ለፍቅረኛቸው እንደማይመጥኑ አድርጎ የማሰብ ነው።

“በሴቶች ላይ የግንኙነት ጭንቀት መገለጫው ግንኙነት ማድረግ አለመፈለግ፣ ስሜት ውስጥ መግባት መቸገር፣ ስሜት ጣሪያ ላይ መድረስ ናቸው። በወንዶች ላይ ግን ብልትን ማስነሳትን መቸገር፣ ተነስቶ እንዲቆይ መቸገር፣ ወይም ቶሎ መጨረስ ናቸው። እነዚህ የችግር መገለጫዎች የግብረስጋ ግንኙነት ጭንቀት ተብለው ይጠቃለላሉ።”
– ክላውዲያ ሲክስ

ጭንቀት የሚሰማን ለምንድን ነው? ነገሮች የሚወሳሰቡት እዚህ ላይ ነው። አልጋ ውስጥ ፍቅረኛችንን ማስደሰት የማንችል ሲሰማን ወይንም ገጽታችን ለፍቅረኛችን አይስብም ብለን ካሰብን ወይንም ከአንድ ሰው ጋር የምናደርገው የጋለ ቅርበት ሊያስፈራን ይችላል።

አንዳንድ ግዜ የግብረስጋ ግንኙነት ጭንቀት መንስኤው ድሮ ያጋጠመን ጥቃት ሊሆን ይችላል። የችግሩ መንስኤ ይህ ከሆነ የአእምሮ ሃኪም ማማከር ተገቢ ነው።

እንደ ግብረስጋ ግንኙነት አማካሪ ኤሚ ጎዳርድ ከሆነ ግን አብዛኛው ግዜ የችግሩ መንስኤ ለራሳችን የምንሰጠው ግምት ነው። ከታች ይህንን ችግር ልንቀርፍበት የምንችልባቸውን መንገዶች እንመለከታለን።

በሰውነትዎ መተማመን

lightstargod / Pixabay

ለራሳችን ሰውነት ያለን ግምት ዝቅተኛ ከሆነ የግብረስጋ ግንኙነት ህይወታችንን ሊያውክ ይችላል። በሰውነታችን ካፈርን ፍቅረኛችን ይጠየፉብናል ብለን እንገምታለን። በዚህ ስሜት ውስጥ ሁኖ ግንኙነት ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ ለመገመት አይከብድም።

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ብዙ ወንዶች እና ሴቶች በራሳቸው ግጽታ አይተማመኑም። ይህም ወደ ግንኙነት ጭንቀት ሊወስደን ይችላል።

የሰውነትዎ ገጽታ አጥጋቢ አይደለም ብለው ካሰብ ምን ማድረግ ይችላሉ። እንደ ግንኙነት አስተማሪ ኤምሊ ናጎስኪ በራስዎ ቆዳ እንዲመቻቹ ተገቢውን እርምጃዎች መውሰድ አለብዎ። ከሰውነትዎ የሚወዱትን ነገር እያነሱ ደጋግመው እራስዎን ማስታወስ አለብዎ።

የሚከተለውን ምክር ትሰጣለች፦

“ባዶ ገላዎን ሁነው መስታወት ፊት ይቁሙ። የሚያዩትን ነገር በደንብ አስተውለው የሚወዱትን ነገሮች በሙሉ ይዘርዝሩ። ነገም ከነገወድያም እያሉ ይደጋግሙት።” እንደ ናጎስኪ ከሆነ መደጋገሙ የራስዎን ሰውነት እንዲለምዱ እና በራስዎ እንዲተማመኑ አስፈላጊ ነገር ነው።

የግብረስጋ ግንኙነት መንገዶችን ይወቁ

Prinz-Peter / Pixabay

ሌላኛው ግብረስጋ ግንኙነት እንዲጨንቅዎ የሚያረግ ነገር ስለ ግንኙነት በቂ እውቀት አለመያዝ ነው።

ይህ ማለት ምን የት መግባት እንዳለበት አያውቁም ማለት ሳይሆን በግንኙነት ወቅት ለሚፈጠሩ ለሚችሉ ነገሮችን ዝግጁ አይደሉም ማለት ነው። እውነታው ሁሉም ሰው በግንኙነት ላይ የተለያየ ፍላጎት አለው።

ለፍቅረኛዎ ደስታን የሚሰጡበትን መንገዶች ጠንቅቀው አያውቁም ይሆናል። ወይንም ስለ ግንኙነት እውነት ያልሆኑ ነገሮችን ሰምተው ይሆናል። ወይንም የራስዎ ስሜት እና ፍላጎት ወጣ ያለ ነው ብለው አፍረው ይሆናል።

ስለዚህ ጉዳይ ማንኛውም አይነት ጥያቄ ካለዎት የግንኙነት መጽሃፍ ማንበብ ካልሆነም በጉዳዩ ዙርያ የሚሰራ የጤና አማካሪ ማማከር ተገቢ ነው።

የግንኙነት ባለሙያ ጎዳርድ እንዲህ ስትል ትናገራለች፦

“ትልቅ ሰዎችም የግብረስጋ ግንኙነት ትምህርት ያስፈልጋቸዋል። የሆነ ቦታ ካልተማርነው እንዴት የሚያስደስት አይነት የግንኙነት ህይወት ይኖረናል? መስተካከል እንደማይችሉ ለራስዎ መንገር ያቁሙ። የሚገባዎትን እውቀት በሚገባው ግዜ አላገኙ ይሆናል”
– ኤሚ ጆ ጎዳርድ

የራስዎንም ሰውነት እየዳበሱ ምን እንደሚያስደስትዎ በማጥናት እራስዎንም ማስተማር ይችላሉ። ግዜ ወስደው ምን እንደሚፈልጉ እና እንዴት እንዲደረግልዎ እንደሚፈልጉ ያጤኑ።

እራስን በራስ ማስደሰት እስካሁን እንደመጥፎ እና አሳፋሪ ነገር ቢሆንም የሚታየው የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚናገሩት በራሳችን ሰውነት ያለንን መተማመን በመጨመር የግንኙነት ህይወታችንን እንደሚያግዝ ይነገራል።

ምን እንደሚፈልጉ ለፍቅረኛዎ ይንገሩ

27707 / Pixabay

ምን እንደሚያስደስትዎ ካወቁ በኋላ ፍላጎትዎን ለፍቅረኛዎ መናገር አስፈላጊ ነው። አብሮዎት ያለውን ሰው ካመኑት ምን እንደሚያስደስትዎ መናገር ይገባዎታል።

የሚፈልጉዋቸውን ነገሮች መግለጽ ልማድ ማድረግ ለግንኙነታችሁ ከፍተኛ ጥንካሬ ይሰጠዋል። በግንኙነት ግዜ ሲቸገሩ ከፍቅረኛዎ ጋር የሚሰማዎትን መግለጽ ችግርዎን የሚቀንሱበት ዋና መንገድ ነው።

በጆርናል ኦፍ ማርሻል ኤንድ ፋሚሊ ቴራፒ በተባለ የምርምር መጽሄት የታተመ ጥናት 142 ፍቅረኛሞች ላይ ምርምር አድርጓል። የጥናቱ ግኝት እንደሚናገረው ያለጭንቀት የግንኙነት ፍላጎታቸውን የሚነጋገሩ ጥንዶች ይበልጥ ጤነኛ እና ደስታ የተቀላቀለበት የግንኙነት ህይወት እንደሚያሳልፉ ይናገራል።

ጥናቱን ያካሄዱት ተመራማሪዎች እንደሚሉት “ፍላጎታቸውን የሚያካፍሉ ሴቶች ይበልጥ የስሜት ጣሪያ ይደሳሉ።” የግንኙነት ፍላጎትን ግልጽ ማድረግ የተሻለ ግንኙነት እንደሚፈጥር ተመራማሪዎቹ ጨምረው ይናገራሉ።

የግንኙነት አማካሪ ሲክስ በግንኙነት ወቅት እራስዎን ዝቅ አድርገው እንዳይመለከቱ ታሳስባለች። “ለራስዎ ስሜት ቦታ ሊኖር ይገባል” ስትል ትመክራለች። ቀጥላም በግንኙነት ግዜ “ድምጻችንን ማሰማት” እንዳለብን ትመክራለች።

በግንኙነት ወቅት በመሃከላቹህ ጭንቀት ካለ መነጋገርን መለማመድ ይህንን ሁኔታ እንደሚያጠፋ ትናገራለች።

ከምንም በላይ ማስታወስ ያለብዎ ነገር ፍቅረኛዎ ከእርስዎ ጋር ግንኙነት መፈጸም እንደሚፈልጉ ነው። ፍቅረኛዎ የእርስዎን ፍላጎት ማሟላት ይፈልጋሉ። እየተነጋገሩ ቀስ በቀስ መመቻቸት ይችላሉ።

Tenegna

አነጋግሩን

ከእርስዎ መስማት እንፈልጋለን። እባክዎ አነጋግሩን።

በጣም የታዩ