ጤነኛ

አዲስ ጥናት፦ ደስተኛነትን ለማግኘት መጣር ጉዳቱ ሳያመዝን አይቀርም

ደስተኛ መሆን። ሁሉም ሰው የሚፈልገው ነገር ቢኖር እሱን ነው። ሰአቶቻችንን በሙሉ ደስተኛ የሚያደርጉንን ነገሮች ፈልገን ልንሰራ እንችላለን። ነገር ግን ውጤቱ የምንፈልገው አይነት ላይሆን ይችላል።

አብዛኞቻችን ያደረግነው ነገር ነው። ትምህርት ቤት እንሄዳለን። ጨርሰን ከተመረቅን በኋላ ደስተኝነትን እናገኛለን ብለን እናስባለን። እንደተመረቅን ግን ደስተኛነት ገና ርቆ እናገኘዋለን።

ከዛ ደግሞ የምንፈልገውን ስራ ስናገኝ በስተመጨረሻ ደስተኛ እንሆናለን ብለን እናስባለን። ስለዚህ ግዜአችን እና ሃይላችንን ተጠቅመን የምንፈልገውን ስራ እናሳድዳለን። አንዳንዴም ይሳካልናል። ከዛ ግን እንደገና ደስተኛነትን አለማግኘታችን ይሰማናል። እያለ እያለ ህይወታችን ይቀጥላል።

ደስተኛነትን እንደአላማ መያዝ በአሁኑ ግዜ በጣም እየተለመደ የመጣ ክስተት ነው። ምንም እንኳ ደስተኛነት ተጨባጭ ያልሆነ ስሜት ቢሆንም ሁላችንም እንመኘዋለን። ጉግል ላይ ተፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ስናይ “እንዴት ደስተኛ መሆን ይቻላል” የሚለው ጥያቄ ባለፉት 5 አመታት ከፍተኛ እድገት አሳይቷል።

ሌሎች ተፈላጊነታቸው የጨመሩ ጥያቄዎች ውስጥ “ደስተኛነት ባላገኝ እንኳ እንዴት ሃዘን መቀነስ እችላለሁ” የሚለው ጥያቄ ይገኝበታል። ይህ ደስተኛነትን የማግኘት ጥረት አእምሮአችን ላይ ምን ተጽእኖ ይኖረው ይሆን? አዲስ የሚወጡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ደስተኛ ለመሆን የሚደረግ ከፍተኛ ጥረት ደስታችንን ይበልጥ ያርቁታል።

ሳይኮኖሚክ ቡለቲን ላይ የታተመ አዲስ ጥናታዊ ጽሁፍ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡

“ሰዎች ደስተኛነት እንዲሰማቸው ይፈልጋሉ እና ይሞክራሉ። ደስተኛም ሁነው ራሱ ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን ይጥራሉ።”

የረትገርስ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ አይክያንግ ኪም እና የቶሮንቶ ዩኒቨርስቲው ተመራማሪ ሳም ማጂሎ ደስተኛነትን እንደ እቅድ መያዝ በአእምሮ ላይ ያለውን ተጽእኖ ሲያጠኑ ቆይተዋል።

ተመራማሪዎቹ ደስተኛነትን እንደ እቅድ መያዝ የግዜ አስተሳሰባችንን እንዴት እንደሚቀይረው አጢነዋል።

ደስተኛነትን የማግኘት ድካም

saschamilk / Pixabay

በጥናቱ የተመረመሩት ሰዎች መጀመረያ ላይ የጽሁፍ ቃለ መጠይቅ እንዲሞሉ ተደረጉ። ደስተኛ ለመሆን ያላቸውን ፍላጎት እንዲሁም በህይወታቸው ግዜ እያመለጣቸው መስሎ እንደሚሰማቸው ተጠየቁ።

ከመልሳቸው መረዳት እንደተቻለው አንድ ሰው ደስተኛነትን እንደእቅድ ከያዘ ህይወት እያለፈው እንደሚመስለው ተረጋግጧል።

ተመራማሪዎቹ ባደረጉት ሁለተኛ ጥናት ተመርማሪዎቹን ሁለት አይነት ፊልም እንድያዩ አደረጉ። አንዱ አስቂኝ ፊልም ሲሆን ሌላኛው ምንም ስሜት የማይሰጥ ፊልም ነበር። ፊልሙን ሲያዩ ግማሾቹ እያዩ እንዲደሰቱ ተነገሯቸው ነበር። ግማሾቹ ደግሞ እንደተሰማቸው እንዲሆኑ። ደስታ እንዲሰማቸው የተጠየቁት ከሌሎቹ ጋር በንጽጽር በቂ ግዜ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።

ሌላም ባደረጉት 3ኛ ሙከራ ተመራማሪዎቹ ኪም እና ማጂሎ ተመሳሳይ ውጤት ማረጋገጥ ችለዋል። እራሳችንን ደስተኛ ለማድረግ በጣርን ቁጥር ደስተኛ ለመሆን ግዜ ያጠረን ይመስለናል። ግዜ ያጣን በመሰለን ቁጥር ደግሞ ይባስ ደስታ እናጣለን።

“ደስታ ስናሳድድ ግዜ የጠፋብን ነው የሚመስለን” ሲሉ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።

ደስተኛነትን እንደ እቅድ መያዝ የለብንም

ለዚህ እንደመፍትሄ ያስቀመጡት ደስተኛነትን እንደ እቅድ ከመያዝ ይልቅ ግዜአችንን ህይወታችንን በማጣጣም ለማሳለፍ መሞከር ነው።

እንደ ተመራማሪዎቹ፡

“ሰዎችን ስለደስታ ማሰብ እንዲቀንሱ በማበረታታት የበለጠ የግዜ ስሜት እንዲሰማቸው እንዲሁም ከተሳሳት የደስታ ፍለጋ መንገድ እንዲወጡ ይረዳቸዋል።”

Tenegna

አነጋግሩን

ከእርስዎ መስማት እንፈልጋለን። እባክዎ አነጋግሩን።

በጣም የታዩ